EthiopiaNews

ኢዜማ በድምሩ 86 መቀመጫዎችን በማግኘት በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚው ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ አጠናቋል።

ኢዜማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንትና ይፋ ባደረገው የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ውጤት 13 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 73 የክልልና የከተማ ምክር ቤት ወንበሮችን ማግኘቱን ጠቁሞ ምርጫው ከነእንከኖቹም ቢሆን በሰላም በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አለን ብሏል።

ፓርቲው የምርጫውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ባሉት ዓመታት ጠንካራ ጎኖቹን በማስቀጠል እንዲሁም የነበሩበትን ክፍተቶች በስትራቴጂ እና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራት በመሙላት ተጨባጭ የተፎካካሪ ፓርቲነት ሚናውን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡

በመጪዎቹ ዓመታት ከዚህ ቀደም ስናደርገው እንደነበረ ሁሉ ብሔራዊ ጥቅሞችን በሚያሣኩ ጉዳዮች ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃይል ጋር በመተባበር እንሰራለን ያለው ፓርቲው የጀመርነውን ጤናማና ዘመናዊ የፖለቲካ ባሕል በተጠናከረ መልኩ እንደምንቀጥል ቃል እንገባለን ብሏል፡፡

ኢዜማ ይህን ስኬት ላስመዘገቡ የፓርቲው ዕጩዎች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች እና በሂደቱ በቅንነት ለተሳተፉ አካላት ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv