EthiopiaNews

የዓለም ባንክ ድጋፍ ለኢትዮጵያ

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የሪፎርም ጥረትን እንደሚደግፍ አስታወቀ።

ባንኩ ይሄን ያለው በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ጉባኤ ላይ ነው።

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ከስብሰባው ጎን ለጎን፣ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቤርዴ ጋር ውይይት አድርጓል።

ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደትና እያጋጠሙ ያሉ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖዎችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፤የልማት ስኬቶችን ዘላቂ ለማድረግ የዓለም ባንክ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ የዓለም ባንክ የፋይናንስ አቅርቦቱን እንዲያሰፋና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የድጋፍ ማዕቀፍ እንዲዘረጋ ጠይቀዋል።

የዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቤርዴ በበኩላቸው ባንኩ ለኢትዮጵያ ያለውን ጽኑ አጋርነት ያረጋገጡ ሲሆን፤ በዚህ ወሳኝ ወቅት ከልማት አጋሮች ጋር በመቀናጀት ተቋሙ ድጋፉን ይበልጥ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ልዑክ በዕዳ ሽግሽግ ሂደቱ የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፤ የዕዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ከግል አበዳሪዎች ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት ውጤታማ መሆኑን ገልጿል።

ሁለቱም ወገኖች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ቤተሰቦችን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማስፋት እና የአገሪቱን የኢኮኖሚ ለውጥ ለማራመድ ያለመ “ሚሽን 300” የኢነርጂ ተነሳሽነትን ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን አስፈላጊነት እና ቁርጠኝነት አጉልተው ገልጸዋል።

መረጃው ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ ነው።

#EBS
#EBSTVNEWS
#EBSTVSPORT
#_7696_WN
https://t.me/ebstvnews
www.ebstv.tv