ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ከግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በነበሩት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ከተሞች ላይ ባደረገው ድንገተኛ የቁጥጥር ስምሪት ሲሆን በነዳጅ ማደያዎች የመቅጃ ማሽን ላይ ምርመራ ባደረገበት ወቅት የማደያዎቹ ማሽኖች ትክክለኛውን ልኬት የማያሳዩና የነዳጅ ቅሸባ የሚፈፀምባቸው ናቸው ብሏል።
በዚህም ከሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ጥፋታቸው መጠን ከአንድ ወር እስከ ሁለት ወር የነዳጅ ጭነት ዕገዳ ማድረጉን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ለኩባኒያዎች በፃፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡
በዛሬው እለትም 3 ማደያዎች የሁለት ወር እና 1 ማደያ የአንድ ወር የነዳጅ ጭነት ዕገዳ የተጣለባቸው ሲሆን 6 ማደያዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በተመሳሳይ የምርመራ ሪፖርታቸው እየተዘጋጀ ባሉ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ማደያዎች ዝርዝራቸውን በቀጣይ ቀናት የሚያሳውቅ መሆኑን ባለስልጣኑ ጨምሮ ገልጿል፡፡
በቀጣይም የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ድርጊታቸው በማይታቀቡት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስቧል።
ተገልጋዩ ሕብረተሰብም በዚህና መሰል የሆኑ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚፈጸሙ ጥፋቶች ሲያጋጥሙ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስተያያትና ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል።
