አምራች ወይም ላኪዎች ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው የቀረጥ ነጻ ወይም ቀረጥ ቅናሽ ስምምነቶች ተጠቅመው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ሃገራት መሸጥ የሚያስችላቸውን ፈቃድ የሚያገኙበት አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የዕቃዎች ስሪት ሀገር ቅደመ መረጃ አሰጣጥ መመሪያ መሰረት ላኪዎች ምርት የመላክ ሂደት ከመጀመራቸው በፊት በቀረጥ ነጻ ስምምነቶች የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ ፈቃድ የሚሰጥ መሆኑንም አስፍሯል፡፡
መመሪያው ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው የቀረጥ ነጻ የንግድ ስምምነቶችን ለመጠቀም ወደ ውጭ ሀገር በሚላኩ ዕቃዎች ላይ ሁሉ ተፈጻሚ የሚደረግ ሲሆን ላኪዎች የፈቃድ ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉት ዕቃውን የመላክ ሂደት ከመጀመራቸው በፊት ብቻ መሆን እንዳለበትም ተገልጿል፡፡
ድርጅቶች ይሄን ፈቃድ መጠየቅ የሚችሉት ለአንድ ዕቃ ብቻ መሆኑ በመመሪያው የተቀመጠ ሲሆን እቃው የሚላክበትን ሀገር፣ የእቃው ሙሉ መግለጫ፣ እቃውን ለመስራት ግብአት የሆኑ የጥሬ እቃዎች ዝርዝርና የእቃውን የአመራረት ሂደት ማሳወቅ እንደሚኖርባቸውም ጠቅሷል፡፡
የስሪት አገር ቅድመ መረጃ ጥያቄ የቀረበበት ዕቃ ከሀገር እንዳይወጣ በህግ የታገደ ከሆነ፤ ዕቃው በኮሚሽኑ የቅሬታ ሂደት ላይ የሚገኝ ከሆነ ወይም ከኮሚሽኑ ውጭ በፍርድ ቤት ወይም በነጻ ንግድ ስምምነት የጭቅጭቅ አፈታት ሂደት ላይ ያለ ከሆነ ፈቃድ እንደማይሰጥም ተጠቅሷል፡፡
