ሚኒስትሯ ይሄን ያሉት በዛሬው ዕለት በከፍተኛ ድምቀት መከበር በጀመረው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ላይ ነው።
ዶ/ር መቅደስ ላለፉት 100 ዓመታት ተቋሙ የሳይንሳዊ ብቃት፣ የፈጠራ ሥራ እና የሀገር አገልግሎት ጠንካራ ምሰሶ ሆኖ መቆየቱን ገልፀዋል።
ሚኒስትሯ ተቋሙ በበሽታ ቅኝትና ክትትል፣ በላቦራቶሪ አገልግሎቶች፣ በምርምር፣ በህብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ እንዲሁም በሥነ-ምግብ እና በህዝብ ጤና መረጃ ሥርዓቶች አማካኝነት የኢትዮጵያን ህዝብ ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከሚገኙ ቀዳሚ የህዝብ ጤና ተቋማት አንዱ ነው ብለዋል።
ዶ/ር መቅደስ የህዝብ ጤና ተግዳሮቶች የሆኑትን አዳዲስና ተመላላሽ ተላላፊ በሽታዎች፣ የፀረ-ተዋህሲያን መድሀኒቶችን መቋቋም፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሥነ-ምግብ ችግሮች እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመመከት ይቻል ዘንድ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ተቋሙ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ታኅሣሥ 1924 በአዲስ አበባ ጉለሌ አካባቢ በሚገኘው በተፈሪ መኮንን ሆስፒታል ውስጥ እንደ አነስተኛ የክሊኒካል ላቦራቶሪ ዉስጥ መመስረቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። መረጃው ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኘ ነው።
