ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚመካከሩበት ታሪካዊ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እንዲሳካ ዜጎች ራሳቸውን ከሀሰተኛ መረጃ መጠበቅ አለባቸው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ህብረተሰቡ በኮሚሽኑ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና በዚህም ራሳቸውን ከሃሰተኛ መርጃ ይጠብቁ ብሏል፡፡
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረውን ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በተመለከተ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች አማካኝነት ከእውነታ የራቁ መረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ደርሼበታለሁ ነው ያለው ኮሚሽኑ።
ኮሚሽኑ የመናገር ነጻነትን ሙሉ በሙሉ የሚያከብር ገለልተኛ ተቋም እንደመሆኑ ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችንና ውይይቶችን የሚቀበል ቢሆንም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀሰተኛ መረጃዎች እንዳይታለል አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ይገደዳል ብሏል፡፡
የዚህ ሂደት ስኬት የሚወሰነው ዜጎች በትዕግስት፣ በጥበብ እና በጋራ የኃላፊነት ስሜት ለመሳተፍ በሚያሳዩት የጋራ ቁርጠኝነት ላይ ነው፣ ይህም እየተከናወነ ይገኛል ያለው ኮምሽኑ ሂደቱ ተጀመረ እንጂ ውጤቱ ገና በመሆኑ ይህንን ውጤት በትዕግስት መጠበቅ ደግሞ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠበቅ መሆኑን አሳስቧል፡፡
በዚህ መሰረት ባለፉት አራት ቀናት ኮሚሽኑ የጉባኤው ተሳታፊዎች የተጣለባቸውን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ማድረግን ጨምሮ ለሂደቱ ጠቃሚ በሆኑ የእውቀት እና የስነ-ልቦና ዝግጅቶች እንዲያደርጉ መደላድሉን ፈጥሯል፤ ይህም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው አንድ አካል መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
