EthiopiaNews

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ በበጀት ዓመቱ ከ27.5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የተኪ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከ26.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምርት በኮርፖሬሽኑ በሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ ባለሀብቶች ተመርቶ ለገበያ መቅረቡን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ለሀገር ውስጥ ገበያ የቀረቡት ምርቶች ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸሩ 44 በመቶ ዕድገት አስመዝግበዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ከልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ መካከል ቦሌ ለሚ፣ አዳማ እና ደብረ ብርሃን ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከፍተኛውን የተኪ ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ቀዳሚ ደረጃን መያዛቸውን አመላክተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኩባንያዎች ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቧቸውን ምርቶች ይበልጥ እንዲያሳድጉና የምርት አቅርቦቱም በቀጣዩ በጀት ዓመት በተመሳሳይ መልኩ እንዲቀጥል በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

በአርሶ አደሮች፣ በአምራቾችና በኩባንያዎች መካከል በተፈጠረው የገበያ ትስስር ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንግድ ግብይት እንዲፈጸም ማስቻሉን የገለጸው ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኮርፖሬሽኑ በሚተዳደሩ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ ባለሀብቶች ተመርተው ወደ ውጭ ገበያ ከተላኩ ምርቶች ከ266 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ንግድ ገቢ ተገኝቷል ብሏል።