EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ባካሄደው በግንዛቤ የተደገፈ የተጠናከረ ቁጥጥር ካለፈው 2017 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የመንገድ ተጠቃሚውን ከትራፊክ አደጋ መከላከል መቻሉንና የደንብ ተላላፊዎችም ቁጥር መቀነሱንም ገልጿል፡፡

ይህንንም በቁጥር ሲያስረዳ ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር  የደንብ ተላላፊዎች ቁጥር ከ53 በመቶ ወደ 45 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስረድቷል፡፡

አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከርንም ረገድ ደግሞ በ2017 በጀት ዓመት አልኮል ጠጥተው ሲያሽከረክሩ የተገኙ አሽከርካሪዎች ከ4 ሺህ 236 በላይ ሲሆኑ በ2018 ደግሞ 3 ሺህ 356 ያህል እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ስልክ እያነጋገሩ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች በ2018 የበጀት አመት 10 ሺህ 334 ያህል መሆናቸው ተገልጾ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 7.5 በመቶ   እንደቀነሰ ተመላክቷል፡፡

የደህነነት ቀበቶ ሳያስሩ ወይም አብሮ የተሳፈረው ሰው ማሰሩን ሳያረጋግጡ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች በቁጥር 3 ሺህ 172  ያህል እንደሆኑና ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር 41% መቀነሱም ተገልጿል፡፡

እንዲሁም መሰረተ ልማት በተሟላባቸው የእግረኞች መንገዶችን ባለመጠቀም በ2018 በጀት ዓመት ወደ 60 ሺህ 842 ያህል እግረኞች መመዝገባቸውን ነው የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የገለጸው፡፡