EthiopiaNews

በአዲስ አበባ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ፤ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ እና በዜጎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ተገለፀ፡፡

የአከራዮችን እና ተከራዮችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ነው የተባለው ይህ አዋጅ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ሳያስመዘግቡ መከራየትና ማከራየትን የሚከለክል ነው፡፡

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል የኪራይ ዘመኑ ሳይጠናቀቅ በአከራዩና ተከራዩ ስምምነት፣ ተከራይ ቤቱን መልቀቅ ሲፈልግ የሁለት ወር የቅድሚያ ማስታወቂያ በመስጠት ወይም የቤት ባለቤትነት በሕጋዊ መንገድ ለሌላ ሰው ሲተላለፍ የ6 ወር ማስጠንቀቂያ በመስጠት ሊቋረጥ ይችላልም ነው የተባለው።

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል እድሳት አለማስመዝገብ፤ በአዋጁ ከተፈቀደው አግባብ ውጪ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፤ በባንክ ወይሞ በሌላ ሕጋዊ በሆነ የኤሌክትሮኒክ የክፍያ ስርዓት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ክፍያ አለመፈፀም በአዋጁ የተከለከለ ነው፡፡

ቀደም ሲል ሲከራይ የቆየ የመኖሪያ ቤት ወይም ግንባታው ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ አዲስ መኖሪያ ቤት ያለ አገልግሎት እንዲቀመጥ ማድረግም ፈፅሞ የተከለከለ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡