በ2018 በጀት አመት በአዲስ አበባ ከተማ ከ385 ሺህ በላይ ልደት፣ ከ40 ሺህ 600 በላይ ጋብቻ፣ ከ9 ሺህ 5መቶ በላይ ፍቺ እንዲሁም ከ22 ሺህ 9መቶ በላይ ሞት መመዝገቡ ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው የከተማዋ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ በ2018 በጀት አመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይ ነው።
በተጠናቀቀው የበጀት አመት በአጠቃላይ ከ2.4 ሚሊየን በላይ አገልግሎቶች መሰጠታቸውን የገለጹት የኤጀንሲው ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮሴፍ ንጉሴ ካላገባ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ደግሞ ለ136 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡
ኤጀንሲው ቀደም ሲል በቢሮ ደረጃ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለመቀየር ያለመ በርካታ ስራዎች ማከናወኑንም ነው ያስታወቀው።
በተጨማሪም ዜጎች “ፋይሌ ጠፍቷል” በሚል የሚያቀርቡትን ቅሬታ ለመቀነስ 12 ሚሊዮን የነዋሪዎች ሰነዶችን ስካን በማድረግ ወደ ዲጂታል ሰነድ አስተዳደር ስርዓት ማስገባት መቻሉ በመግለጫው ተነስቷል።
በተቋሙ ብልሹ ተግባራትን በማጋለጥ ተጠያቂነት ለማስፈን በተወሰዱ እርምጃዎች ደግሞ በበጀት ዓመቱ ውስጥ 13 አመራሮች፣ 78 ፈጻሚ እና 14 ባለጉዳይ በድምሩ 105 ሰዎች ተጠያቂ ተደርገዋል ነው የተባለው፡፡
ቤዛዊት መኮንን ዘግባለች፡፡
