ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው 49ኛው የአፍሪካ ህብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ሚኒስትሩ በንግግራቸው ጉባኤው የዓለም አቀፍ ሥርዓትና የጂኦፖለቲካዊ አወቃቀሮች ጥልቅ ለውጥ እየታየባቸው ባሉበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ጌዲዎን የጂኦፖለቲካ ውድድር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች እንዲሁም ስልታዊ በሆኑ ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ላይ እየተካሄደ ያለው ውድድር አዲስ የዓለም አቀፍ ሥርዓት እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው አፍሪካ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለዓለም አቀፍ ፈተናዎች አፍሪካውያን መፍትሔዎችን ማቅረብ የምትችል ሥትራቴጂካው ተዋናይ መሆን እንዳለባት አሳስበዋል።
ሚነስትሩ አክለውም አፍሪካ ህብረት የአህጉሪቷን ቅድመ-አጀንዳዎች የሚያስፈጽም፣ መብቷን የሚያስከብርና ተስፋ ሰጪ ድምፅ ሆኖ መውጣት እንዳለበት ገልጸዋል።
አህጉሪቷ እ.ኤ.አ. በ2026 ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ የዓለም 10 ሀገራት መካከል ስምንቱን ያቀፈች በመሆኗ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ሞተር እንደምትሆን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ አንድነትና ጥንካሬ ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሩ ህብረቱ ውሳኔዎቹን በተግባር ለመተርጎም የሚያስችለውን የራሱን ዘላቂና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ማረጋገጥ፣ የጋራ ሀብቶችን በትብብር፣ በፍትሃዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት ለአህጉራዊ ትስስርና ብልጽግና ማዋል፤ ችግሮችንም በአፍሪካውያን ተቋማትና ማዕቀፎች መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።መረጃው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ ነው።
