EthiopiaNews

የትምህርት ሚኒስቴር ባለፉት አመታት ተቋርጦ የነበረው የመምህራን የክረምት የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ስልጠና በዚህ ክረምት በስምንት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ ገለጸ፡፡

በማስተማር ሥራ ላይ ያሉ መምህራንን ከዲፕሎማ ወደ መጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ስልጠና ለመጀመር በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቅድመ ዝግጅት ስራውን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

በዚህም ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የተናበበ የሥልጠና ማዕቀፍ፣ ፕሮግራሙን ለመምራት የሚያስችሉ የትግበራ ሰነዶችንና የሰልጣኝ መምህራንን ምልመላ፣ መረጣ እና ምደባ መከናወኑን ጠቅሷል፡፡

ስለሆነም ባለፉት አመታት በስልጠናው አሰጣጥ ጥራት ችግር ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመምህራን የክረምት የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ ስልጠና በዚህ ክረምት በባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ፣ ጂማ፣ ሃሮማያ፣ ጎንደር፣ አርባ ምንጭ እና ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

በ2018 ዓ.ም ክረምት 8,273 መምህራንን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ወደ ስልጠና እንደሚገቡም ነው የተጠቀሰው፡፡

በዚህ መሰረት የመግቢያ ምዘና ወስደው ያለፋ እና በየዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ሰልጣኝ መምህራን ምዝገባ ሐምሌ 24 እና 25/2018 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በተጠቀሱት ቀናት በተመደቡበት ዩኒቨርስቲዎች በመገኘት እንዲመዘገቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ሰልጣኞች ይህንን https://shorturl.at/ZjN9e ማስፈንጠሪያ በመጫን የተመደባችሁበትን ዩኒቨርስቲ ማወቅ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።