የዘንድሮው ክረምት ከገባ ጀምሮ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
በትናትናው ዕለት በአንድ ጀምበር 805 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ያስታወቀው ተቋሙ በዚህ መርሃ ግብር ላይ 26 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን ገልጿል።
በዚህም በዘንድሮው ክረምት በአጠቃላይ 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መንግሥት ያስቀመጠውን እቅድ ለመፈጸም ህዝቡ ቁርጠኛ መሆኑን በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የአንድ ጀምበር መርሃ ግብር ላይ አሳይተዋል ነው ያለው።
በሕዝብ ተሳትፎ ታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን ማድረግ መቻሉን የገለጸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለፉት ስምንት ዓመታትም ህዝቡ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፉ 54 ቢሊዮን ገደማ ችግኞችን መትከል መቻሉንም ጠቁሟል፡፡
ይኸው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከ17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ለማድረግ አስተዋፅኦ ከማድረጉ በተጨማሪ የአፈር መሸርሸርን መቀነስና የጠፉ የውሃ ምንጮችን መመለስ ማስቻሉንም ጠቁሟል።
