የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ነፃ ሆኖ የመገመት መብት በዓቃቤ ሕግ ላይ የሚጥለው አነስተኛ የማስረዳት ደረጃ ወንጀሉ በተከሳሹ ስለመፈጸሙ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ የማስረዳት ሸክም ነው በማለት አስገዳጅ የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔ ሰጥቷል።
ምክር ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው ሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በ6ኛው የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በመዝገብ ቁጥር 151 መነሻ ሲሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 3 ሥር የተረጋገጠው ነፃ ሆኖ የመገመት መብት በተግባር ትርጉም እንዲኖረው የተሰጠ ውሳኔ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የሚያቀርበው ማስረጃ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ ማረጋገጥ እንዳለበት በዚህ አንቀጽ ላይ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን ይህ ሳይረጋገጥ የሚሰጥ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሕገ-መንግሥታዊ እንዳልሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ተከሳሽ ጥፋተኛ አለመሆኑን ለማሳየት በዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ላይ ምክንያታዊ ጥርጣሬን መፍጠር ብቻ በቂው እንደሆነና ከዚያ ባለፈ የንጽሕናውን ፍጹምነት የማስረዳት ግዴታ እንደሌለበት በዚህ ውሳኔ መሰረት ተረጋግጧል፡፡
ይህ ውሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔ በመሆኑ በሀገሪቱ በሚገኙ ማናቸውም ፍርድ ቤቶች ላይ የወደፊት የወንጀል ክርክሮችን ለመወሰን የሕግ አስገዳጅነት እንዳለው ነው ምክር ቤቱ የገለጸው፡፡
