EthiopiaNews

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በክረምት ተረኛ ችሎት የሚያስተናግዳቸውን አስቸኳይ ጉዳዮች ይፋ አድርጓል፡፡

በባሕሪያቸው ጊዜ የማይሰጡና አፋጣኝ ውሳኔ ካልተሰጠባቸው ሊካስ የማይችል ጉዳት የሚያስከትሉ አጣዳፊ ጉዳዮችን አይቶ መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ በሚሆኑበት ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በተረኛ ችሎት አገልግሎት ይሰጣል ነው የተባለው።

አስቸኳይ የእግድ አቤቱታዎች፣ የልጅ ቀለብ፣ አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታዎች፣ እንቅስቃሴን ገዳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች እንዲሁም የሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ አፈጻጸሞች፣ ከግልግል ዳኝነት ትዕዛዝ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ አስቸኳይ የማኅተም አገልግሎት ጥያቄዎችና ሌሎች ጊዜ የማይሰጡ ጉዳዮች በተረኛ ችሎት እንደሚታዩም ተገልጿል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ በሚሆኑበት በዚህ ወቅት ተገልጋዮች እና የፍርድ ቤቱ ማኅበረሰብ አሠራሩን ተገንዝበው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጥሪ አቅርቧል።