የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ፋይዳቨርስ በሚል ስያሜ የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ በይፋ ስራ ጀመረ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በትላንትናው እለት ይፋ የተደረገው ፋይዳቨርስ የመንግስት የልማት ድርጅት በመሆን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር እንደገና የተደራጀ ነው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህ ውሳኔ ዲጂታል ማንነት ልክ እንደ መንገድ፣ ኃይል እና ቴሌኮሙኒኬሽን ሁሉ ለኢትዮጵያ ተወዳዳሪነትና ዘላቂ እድገት ወሳኝ የሆነ ስትራቴጂካዊ ሀገራዊ መሰረተ ልማት በመሆኑ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም ፋይዳቨርስ ከሀገር አልፎ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሰረት ለቀጣናው እና ለአፍሪካ አህጉር ልምድና አቅም በማጋራት የአፍሪካ የዲጂታል ሽግግር መሪ እንድንሆን ያስችለናልም ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን መመዝገቡን እና ከ160 ሚሊዮን በላይ የማረጋገጫ አገልግሎቶች መስጠቱንም በንግግራቸው አስታውሰዋል።
