EthiopiaNews

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሌላ ሰው መሬት ላይ ቤት የሠራ ሰው የቤቱ ባለቤት ይሆናል በማለት የተሰጡ የቀደሙ አስገዳጅ ውሳኔዎች ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ናቸው በማለት የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔ ሰጥቷል።

ምክር ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው ሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በ6ኛው የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በመዝገብ ቁጥር 151 መነሻ ሲሆን በመንግሥት አካል ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተሰጠው ሰው፣ የመሬቱ ሕጋዊ ባለይዞታ የመሆን እና በመሬቱ የመጠቀም ሕገ መንግሥታዊ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡

በዚህም መሰረት አንድ ሰው የሌላ ሕጋዊ ባለይዞታ በሆነ መሬት ላይ ባለይዞታው ሳይቃወመው እንኳን ቢሆን ቤት ቢሠራ፣ የመሬቱ ባለይዞታነት ወይም የቤቱ ሙሉ ባለሃብትነት ወደ ቤቱ ሠሪ እንደማይተላለፍ ነው የገለጸው፡፡

​የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ላይ በመሬት ላይ ንብረት ያፈራ ሰው የንብረቱ ባለቤት ይሆናል የሚለው ድንጋጌ የሚሠራው የመሬት ባለይዞታነት መብት ላለው ሰው እንጂ፣ በሌላ ሰው ይዞታ ላይ ባለ መሬት ንብረት ለገነባ ሰው የቤት ባለቤትነት መብት ለመስጠት አይደለም ሲልም ነው ምክር ቤቱ የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔ የሰጠው።

​ባለይዞታው ሳይቃወም በይዞታው ላይ ቤት የሠራ ሰው የሚኖረው ሕገ መንግሥታዊ መብት ለቤቱ ወይም ለግንባታው ያወጣውን ወጪ ግምት ከመሬቱ ባለይዞታ የመጠየቅ መብት ብቻ መሆኑንም በትርጓሜው ላይ አስፍሯል፡፡