EthiopiaNews

የሕገወጥ ሰዎች ዝውውርን በተመለከተ ጥቆማ ላይ ከተመሰረተ የተጠያቂነት አሰራር አስቀድሞ መረጃ በማሰባሰብ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን ወደማስፈን አሰራር ለመግባት የሚያስችል የአምስት ዓመት የፍልስት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሊጸድቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ የተገለጸው በትላንትናው ዕለት በፍትህ ሚኒስቴር የፍልሰት ትብብር ጥምረት ባሰናዳው የሁለተኛው ፍልስት አስተዳደር ስትራቴጂክ እቅድ ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩም ጥምረቱ ባለፉት አምስት አመታት ሲተገበር የነበረው አገር አቀፍ የፍልስት አስተዳደር ስልታዊ እቅድ ጊዜው በመጠናቀቁ ሁለተኛውን ሲያዘጋጅ መቆየቱን የተጠቆመ ሲሆን ለፍልስት ገፊ የሆኑ ምክኒያቶች ላይ በማተኮር ይሰራል ነው የተባለው፡፡

ከ2019 እስከ 2023 በሚተገበርው በሁለተኛው የፍልስት አስተዳደር ስልታዊ እቅድ እንደ ትምህርትና ግብርና የመሳሰሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የፍልስትን ጉዳይ ጉዳዬ ብለው አቅደው እንዲሰሩበት ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እቅዱ የጉምሩክ ኮሚሽን ባለሙያዎች ኮንትሮባንድ ብቻ ሳይሆን ህገወጥ የሰዎች ዝውውርም የስራቸው አካል አንዲያደርጉ ማስቻል ተካቶበታል፡፡

ይሀው እቅድ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በሚመራው በብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤቱ ቀርቦ በመጽደቅ በቅርቡ ወደትግበራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡