EthiopiaNews

የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ የኮሌራ በሽታን ለማጥፋት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ድርጅቱ ይሄን የገለጸው የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ ኮሌራን የማጥፋት ዕቅድና በተከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ ምክክር እያካሄደ በሚገኝበት መድረክ ላይ ነው።

በዚሁ ጊዜም ከዚህ ቀደም የኮሌራ በሽታን ለመከላከል በተከናወኑ የተቀናጁ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ውጤት መገኘቱን የገለጹት የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መልካሙ አብቴ ለሽታው አፈጣኝ ምላሽ ለመስጠት የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በንጽህና፣ በክትባት እንዲሁም በቅድመ-መከላከል ዘርፍ የተከናወኑት ስኬታማ ተግባራት ኮሌራን ለመቆጠጠር ያስቻሉ መሆናቸውን ጠቁመው ውጤቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በመድረኩ የተገኙት በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋዎች ባለሙያ ኢኖሰንት ኮማኬች በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ኮሌራ የሕብረተሰብ ጤና ሥጋት እንዳይሆን ያከናወነችው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን አንስተው ድርጅታቸው ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ የሚያደርገውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።