ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶች በገበያ ላይ እንዳይቀርቡ ቢከለከሉም የህብረተሰቡን ግንዛቤ መቀየር እንዳልተቻለ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት የሚሰጡና ለአካባቢ ብክለት ዋነኛ መንስኤ እንደሆኑ የለያቸውን የፕላስቲክ ምርቶች ለገበያ እንዳይቀርቡና ምርታቸው እንዲቆም የሚያስገድድ ህግ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል።
ምንም እንኳን ምርቱ እንዲቆም በማድረግ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ቢሆንም፣ እስካሁን የህብረተሰቡን ግንዛቤ መቀየር እንዳልተቻለ የባለሥልጣኑ ዋና አማካሪ አዱኛ ወንድሙ ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ ፌስታል አደገኛ በካይ ቆሻሻ በመሆኑ፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኩል ከተፈቀደው ውጪ ጥቅም ላይ እንዳይውል ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የፕላስቲክ ከረጢት ጥቅም ላይ እንዳይውል በተሰራው ስራ 488 ፌስታል የሚያመርቱ ተቋማት ላይ ክትትልና ቁጥጥር መደረጉን የገለጹት ዋና አማካሪው፤ ተቋማቱ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሊያም በሌሎች ተኪ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን ነው የገለጹት።
