በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአደጋ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ የሌላቸው የህዝብ መገልገያ ህንፃዎች፣ የንግድ ተቋማትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እስከ መቶ ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት አለፍ ሲልም ፍቃዳቸውን እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተነግሯል፡፡
ይህንን ተፈጻሚ የሚያደርገው የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር እና የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በጋራ የሚያስተገብሩት የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ ተግባራዊ መሆን መጀመሩ ተገልጿል፡፡
ይህን አስመልክቶ ሁለቱ ተቋማት ዛሬ በሰጡት መግለጫ የደህንነት ብቃት ማረጋገጫውን ማንኛውም የህዝብ መገልገያ ህንፃ፣ የንግድ ተቋም ወይም አደገኛ ንጥረ ነገሮችን የሚያከማች ድርጅት በየዓመቱ ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመያዝ እና የማደስ ግዴታ ተጥሎበታል።
በደንቡ መሰረትም ተቋማትና የህንፃ ባለቤቶች ደረጃውን የጠበቀ የውሃ መቅጃ ሀይድራንት፣ የእሳት ማጥፊያ ሲሊንደሮች፣ የጭስ ማወቂያዎች የመግጠም እንዲሁም በህንፃ ዲዛይኖቻቸው ውስጥ የአደጋ ጊዜ ማምለጫ መንገዶችን የማካተትና ክፍት የማድረግ ግዴታ አለባቸው ተብሏል።
የተጣሉ የደህንነት መስፈርቶችን ሳያሟሉ በሚገኙና ህጉን በሚጥሱ አካላት ላይ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ካላሻሻሉ እንደ ጥፋቱ ደረጃ ከ10 ሺ ብር እስከ 100 ሺብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት የሚጣል ሲሆን፣ አለፍ ሲልም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያላስተካከሉ ተቋማት የንግድና ስራ ፈቃዳቸው እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ የሚደረግ ይሆናል ነው የተባለው።
