የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2018 በጀት ዓመት ከ664 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታወቀ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ይሄን ያሉት ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ዋና ሥራ አስፈፃሚ በ2018 በጀት ዓመት አገልግሎቱ 800 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ 664 ሺህ 505 አባወራዎችንና እማወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው የበጀት ዓመት አፈጻፀሙ በተቋሙ ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁመው ይህ አፈፃፀም ተቋሙን ከአፍሪካ መሰል የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያዎች በግንባር ቀደምትነት አንደኛ ያደርገዋል ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚውው የበጀት ዓመቱ አፈፃፀም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ162 ሺህ 917 ደንበኞች ወይም በ32.5 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ገልፀው የተቋሙ አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 5.88 ሚሊዮን በላይ ደርሷል ብለዋል፡፡
ከተጠቃሚዎቹ መካከል 56.8 በመቶ የሚሆኑት የድህረ ክፍያ፣ 43.2 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚ ሆነዋል ተብሏል።
በተጨማሪም በቅርቡ ሥራ ላይ በዋለው የብድር አሰራር 19 ሺህ 231 ደንበኞች ከዋናው ግሪድ፣ 3 ሺህ 364 ደንበኞች ደግሞ ከኦፍ-ግሪድ ከክፍያ ነፃ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸው ተገልጿል።መረጃው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘ ነው።
