EthiopiaNews

ማኅበረሰቡ ሙስናን በማጋለጥና ከሕገወጦች ጋር ባለመተባበር ሀገርን ከሕገወጥነትና ሙስና የመከላከል ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ሕዝቡ በስፋት የሚያነሣቸውን ሌብነትን አስቁሙልን ጥያቄዎች ለመመለስ መንግስት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የገለጹት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ ከንግድ ባንክ ደንበኞች አካውንት ላይ በማጭበርበር ገንዘብ የወሰዱ 36 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ለሕገ-ወጥ ዝውውር ሽፋን ይሰጡ የነበሩ 7 የክሪፕቶ ካረንሲ መተግበሪያዎች እንዳይሠሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ በነበሩ ከ7 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶችና መጋዘኖች ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱንና በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በሐዋላና በጥቁር ገበያ ተሳታፊ የሆኑ 169 ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች በሕግ ተጠያቂ መደረጋቸውን ሚኒስትሯ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

የግብር ውሳኔዎችን በመቀነስ፣ ሐሰተኛ ደረሰኞች በማወራረድና በሲስተም መረጃ በማጥፋት የመንግሥት ገቢን ባሳጡ አካላት ላይ ኦፕሬሽን ተካሂዶ የጥቅም ትስስር የፈጠሩ 91 ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተጠቅሷል፡፡