በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሱና የሀገር ሀብት በሚመዘብሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደ ነው ተባለ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በሰጡት መግለጫ ሕገ-ወጥነትና የሙስና ተግባራት ፈተና ሆነው መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ በተከናወነ ኦፕሬሽን ምዝበራ የፈጸሙና ተቋማዊ አሻጥር በሠሩ አመራሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በዚህ እርምጃም በአፈር ማዳበሪያ ግዢ አሻጥር በፈጸሙ እንዲሁም ተገቢው መመሪያ በሌለበት ሁኔታ የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች ጋር ሕገ-ወጥ የኃይል ሽያጭ ውል የፈጸሙ ከፍተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከነዳጅ አቅርቦትና ሎጂስቲክስ አንጻር ደግሞ 38 የመንግሥት አመራሮችና በሕገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ላይ የተሰማሩ ከ650 በላይ ግለሰቦች፣ ማደያዎችና አቅራቢ ኩባንያዎች ላይ የህግ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሲስተምን በማዛባትና ጉቦ በመቀበል ወንጀል የተሳተፉ 8 ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ነው የተባለው፡፡
