በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ፖሊስ መምሪያ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተሽከርካሪ እቃዎችን በመስረቅ የተጠረጠሩ 5 ግለሰቦችንና የተሰረቁ እቃዎችን ይገዙ የነበሩ 2 ተቀባዮችን በድምሩ 7 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።
ፖሊስ በክፍለ ከተማው በተበራከተው የመኪና እቃ ስርቆት ላይ የተመሠረተ ክትትል ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ለአንድ ወር ከ15 ቀን በተካሄደ ምርመራ ተጠርጣሪዎቹን እንደያዘ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
ፖሊስ በበቂ ማስረጃ የስርቆት ወንጀል ፈጽመዋል ብሎ የጠረጠራቸው 5ቱ ግለሰቦች ዳዊት መንግስቱ፣ከድር አህመድ፣ ማሃዲ ሳቢት፣ ኤሊያስ አረጋ እና በቃሉ አንዱዓለም እንደሆኑ አሳውቋል።
ፖሊስ ደረጀ ታደሰ እና ቾምቤ ሀይሉ የተባሉት ሁለት ግለሰቦች ደግሞ የተሰረቁ የመኪና እቃዎችን ሲገዙ እንደነበር በመረጋገጡ መያዛቸውን አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ቀናትና ቦታዎች ከሌሊቱ 7 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ የመኪና እቃዎችን ሲሰርቁ እንደነበር ምርመራው ማረጋገጡንም ፖሊስ አስታውቋል።
በሸገር ሲቲ ከተማ መልካ ኖኖ ወረዳ ልዩ ቦታው አንፎ በተባለ አካባቢ የተሰረቅ የመኪና እቃ ሲረከቡ የነበሩት ግለሰቦች ሱቅ ላይ በተደረገ ብርበራ የተሽከርካሪ ጌጅ፣ ስፖኪዮ፣ ዳሽ ቦርድ፣ መቁረጫ ከተሮች ፣2 ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች ንብረቶች መያዛቸው ተገልጿል፡፡
ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ መጀመሪያ 11 የምርመራ መዝገቦች የተደራጁ መሆኑን ገልፆ ምርመራው ወደ ቦሌ፣ ለሚ ኩራ፣ የካ፣ አቃቂ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ተስፋፍቶ 10 ተጨማሪ መዝገቦች ተደራጅተዋል ብሏል።
ፖሊስ በድምሩ 21 የምርመራ መዝገቦች የተያዙ መሆኑን ጠቅሶ ክስ ለመመሥረት በሂደት ላይ መሆኑን ፖሊስ ጠቁሟል።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ ጀምሮ በክፍለ ከተማው ይስተዋል የነበረው የመኪና እቃ ስርቆት በእጅጉ መቀነሱ በፖሊስ መግለጫ ተጠቅሷል፡፡
