የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የስራ ጊዜ መራዘሙ ተገለጸ፡፡
በመንግስት ውሳኔ የስራ ጊዜያቸው የተራዘመላቸው የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ለተጨማሪ አንድ አመት እንዲያገለግሉ መወሰኑን ነው የዝግጅት ክፍላችን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ማረጋገጥ የቻለው፡፡
ተራዝሞ የቆየው የዋና ስራ አስፈጻሚው የስራ ጊዜ ባሳለፍነው ሀምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በድጋሚ ተጠናቆ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አየር መንገዱ የጀመራቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከግምት በማስገባት ዳግም የስራ ጊዜያቸው እንዲራዘም መደረጉ ነው የተሰማው፡፡
በቅርቡ የአየር መንገዱን የስራ አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ከዝግጅት ክፍላችን የስራ ጊዜያቸው መጠናቀቅን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላስ የሰጡት አቶ መስፍን በዋና ስራ አስፈጻሚነት የመቀጠልና ያለመቀጠላቸው ጉዳይ የመንግስትን ውሳኔ እንደሚጠብቅ ተናግረው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ተወልደ ገብረማሪያምን በመተካት በመጋቢት 2014 ዓ.ም ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ መስፍን በአየር መንገዱ ከ40 ዓመታት በላይ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡
