EthiopiaNews

በተለያዩ ሀገራት በኢ-መደበኛ ፍልሰት ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ሳልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል ጋር በመተባበር ከስደት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋም የሚያስችል የድጋፍ ስምምነት ኮሚሽኑ ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡

በስምምነቱ ወቅትም የሀገራቱ ታሪካዊ ግንኙነት በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የትብብር መስኮች ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት እየተሸጋገረ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ለአብነትም ከሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት ባሻገር ሕጋዊ የሥራ ስምሪትን በመከተል በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሙያ መስኮች በሳዑዲ ዓረቢያ እየሰሩ መሆኑ ተጠቁሟል።

በመርሃግብሩ ከሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ሳልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል የተበረከቱ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች የድጋፍ ርክክብ ተካሂዷል።