አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ4 የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ሰጥታው የነበረውን በሃገሪቱ የመኖር ጊዜያዊ የከለላ መብት ወይም በምህጻሩ ቲፒኤስ አነሳች።
የትራምፕ አስተዳደር ጊዜያዊ የከለላ መብት ካቋረጠባቸው 4 የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ኢትዮጵያ ፣ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ካሜሩን እንደሚገኙበት ተገልጿል።
አሜሪካ በፈረንጆቹ 2022 አመት በኢትዮጵያ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ለኢትዮጵያውያን ዜጐች ጊዜያዊ የከለላ መብት ሰጥታ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ይህ የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ በአገራቸው ባለው የፀጥታ፣ የጦርነት ወይም የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በአሜሪካ ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ አግኝተው የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ህጋዊ ከለላ የሚነጥቅ መሆኑን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ለ13 ሃገራት ዜጎች ሰጥታው የነበረውን ጊዜያዊ የከለላ መብት ማቆሟን ዘገባው አስታውሷል።
የትራምፕ አስተዳደር የጊዜያዊ የከለላ መብት ስሙ እንደሚገልጸው “ጊዜያዊ” መሆን አለበት በሚል ገልፆ በነዚህ አገራት ያሉ ሁኔታዎች አሁን ላይ ዜጎቻቸው እንዲመለሱ ያስችላሉ በሚል ምክንያት መርሃ ግብሩን አቋርጦታል።
