የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከስምንቱ የሥራ ቡድኖች የተውጣጡ 15 የአጀንዳ ምክረ-ሃሳብ አጠናቃሪዎች ያጠናቀሩትን የአጀንዳ ሃሳብ ለየስራ ቡድናቸው ማቅረባቸውን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ይሄን ያለው የምክክር ሂደቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።
ኮሚሽኑ የእያንዳንዱ የሥራ ቡድን ተወካዮችም የየቡድናቸውን የአጀንዳ ምክረ-ሃሳቦች ድግግሞሽ በማስወገድ፣ ያልተቀናጁ ሀሳቦችን በማደራጀት ወጥ የሆነ ሰነድ አዘጋጅተው ትናንት ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 500 አባላት ላሉት የሥራ ቡድን እንዳቀረቡ ገልጿል።
የተደራጁ አጀንዳዎች የቀረቡላቸው ስምንቱ የሥራ ቡድኖች ሃሳብ እና አስተያየት አክለው የመጨረሻው ሰነድ እንዲዘጋጅ ለአደራጅ ቡድኖቹ መመለሳቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ግብአቶችን የሰበሰቡ የአጀንዳ ምክረ-ሃሳቦችን የሚያጣጥሙ ቡድኖችም የተሰጧቸውን ሃሳቦች በዛሬው የጠዋት መርሃ-ግብር አካተው ለየሥራ ቡድኖቻቸው በከሰዓቱ መርሃ-ግብር በድጋሚ በማቅረብ እንደሚያፀድቁ ይጠበቃል ተብሏል።
500 አባላት ካሏቸው ስምንት የስራ ቡድኖች ከእያንዳንዳቸው 15፣ በድምሩ 120 አባላት ያሉት ቡድን ካለፈው ሐሙስ ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የሥራ ቡድኖች የተነሱ የአጀንዳ ምክረ-ሃሳቦችን በማዳመጥ ወጥ የሆነ ምክረ-ሃሳብ ማቅረብ የሚያስችል ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።መረጃው ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተገኘ ነው።
