በማህበራዊ ሚዲያ አንዲት ታዳጊ ስትደበደብ የሚያሳይ ቪዲዮን በተመለከተ ፖሊስ አስፈላጊውን ምርመራ ማጣራቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
ፈርዶስ መሃመድ ፣ ኤደን ዳዊት እና ሃኒ ሁሴን የተባሉ ታዳጊ ተማሪዎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አለም ባንክ አካባቢ ጓደኛቸውን ሲደበድቧት የሚያሳይ አሳዛኝ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ ድርጊቱን የፈፀሙት ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ ህብረተሰቡ አስተያየት እየሰጠ እንደነበር ፖሊስ አስታውሷል።
ፖሊስ ድርጊቱ ጥቅምት 14 ቀን 2018 አ.ም መፈፀሙን አስታውቆ ቪዲዮው በማህበራዊ ሚዲያ ከመሰራጨቱ ከወራት በፊት ወንጀሉን የፈፀሙትን ሦስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ማጣራቱን ገልጿል፡፡
በወንጀሉ የተጠረጠሩት ሦስት ተማሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው በጊዜ ቀጠሮ ታስረው ፖሊስ አስፈላጊውን ማስረጃ በማሰባሰብ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ መዝገቡን ለሚመለከተው የፍትህ አካል መላኩን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ልጅቷ ስትደበደብ የሚያሳየው ቪዲዮ መለቀቁ በልጅቷም ሆነ በቤተሰቧ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ ቪዲዮውን የለቀቀውን አካል ለማረጋገጥ ፖሊስ ሦስቱን ተጠርጣሪዎች በድጋሚ በቁጥጥር ስር አውሎ ተጨማሪ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡መረጃው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተገኘ ነው።
