የትምህርት ሚኒስቴር የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችን በግልጽ፣ ፍትሐዊና በውድድር ላይ በተመሠረተ ሥርዓት ለመምረጥ የሚያስችለውን አዲስ መመሪያ አጽድቆ ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የቀደመው መመሪያ ክፍተቶች ስለነበሩበት ተቋርጦ እንደነበር የገለጸ ሲሆን አዲሱ መመሪያ ከባለድርሻ አካላትና ከባለሙያዎች ጋር ሰፊ ምክክር ተደርጎበት የተዘጋጀ መሆኑ ገልጿል።
በመጀመሪያው ዙር ትግበራ የወልድያ፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሰላሌ፣ መቱ፣ ወለጋ፣ ድሬዳዋ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ወሎ እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች የፕሬዚዳንትነት ቦታቸውን ለውድድር ክፍት እንደሚያደርጉም ተመላክቷል።
እንዲሁም ከሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎቹ ወደ ውድድር ሂደት እንዲገቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል የተባለ ሲሆን የማስፈጸሙን ኃላፊነት የየዩኒቨርሲቲዎቹ የሥራ አመራር ቦርዶች እንደሚወስዱም ነው የተነገረው።
ሚኒስቴሩ ተወዳዳሪዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን አዲሱ አሠራር ከጊዜያዊ ምደባ ወደ ዘላቂ፣ ግልጽና ፍትሐዊ የአመራር ምርጫ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር መሆኑን ገልጿል።
