EthiopiaNews

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በግሉ ዘርፍ በርካታ ዘመናዊ ሆስፒታሎች መገንባታቸው ለከተማዋ የጤና ዕድገትና ለሜዲካል ቱሪዝም መስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናገሩ።

‎ከንቲባዋ ይሄን ያሉት በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ3 ቢሊየን ብር ካፒታል የተገነባውን የኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስ ትናንት ባስመረቁበት ጊዜ ነው፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደተገኙ ተገልጿል።

በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን ሲመለከቱ ይቆጩ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ ባለፉት ዓመታት በግሉ ዘርፍ ይህን ቁጭት የሚቀይሩ ትላልቅ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

‎አዲስ አበባን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርጉ ትላልቅ ዘመናዊ የጤና ተቋማት መገንባታቸውንም አስታውቀዋል።

‎አዲስ አበባን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስ ተጨማሪ አቅም መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።

ከንቲባዋ ኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስ በኢትዮጲያ ከላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቀጥሎ ሁለተኛው መሆኑን ገልፀው ሆስፒታሉ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት ትልቅ የጤና ማዕከል ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ በከተማዋ የተከናወኑት ተግባራት የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑና ሌሎች ሀገራትም የሚተማመኑበት የጤና ዘርፍ መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመው ይህ በጎ ጅምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።