ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑ በመታመኑ የሃይማኖት አባቶች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 15ኛ የምስረታ በዓል እና 18ኛ ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ጉባኤው ሀገራዊ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የጉባኤውን ያለፉት ዓመታት ጉዞ በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጉባኤው በመላ ሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ያሉ ሲሆን ጉባኤው በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እንዳይፈጠሩ በማድረግ፣ ጥያቄዎች ካሉ ደግሞ በውይይት እንዲፈቱ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ማህበረሰቡን የማቀራረብ እና የማስታረቅ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑን ያስረዱት ዋና ጸሃፊው በጋራ በመስራት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በማመን ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በጋራ በመጓዝ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ግጭት በደረሰባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ በመድረስ እና በማረጋጋት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በማጽናናት ጉባኤው የህዝብ አለኝታ መሆኑን አሳይቷል ያሉት ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጉባኤው ሕዝባዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን በመግለጽ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማዘጋጀት የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
ዋና ጸሃፊው በቀጣይም ጉባኤው ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም በትኩረት እንደሚሰራ በገለጹበት መድረክ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የሃይማኖት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እና አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡
