በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ያለው ግንኙነት ከቀድሞው የተለመደ የልማት ዕርዳታ አሰጣጥ ወጥቶ፣ አሁን ይበልጥ በኢንቨስትመንት ላይ ወደተመሠረተ አጋርነት መሸጋገሩ ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው በአውሮፓ ኅብረት ግሎባል ጌትዌይ ኢኒሼቲቭ እና በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ መካከል ያለው መጣጣም ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ የፖሊሲ ውይይት በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በተካሄደበት መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ ግንኙነቱ በኢንቨስትመንት ላይ ወደተመሠረተ አጋርነት መሸጋገሩን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በመንግሥት ከሚመራ የኢኮኖሚ ሞዴል ወደ የግሉ ዘርፍ የባለቤትነት ድርሻ በሰፊው ወደሚሰፍንበት የገበያ ኢኮኖሚ እየተሸጋገረች መሆኗን የጠቆሙት ዶክተር ዲማ በዚህም ሂደት በርካታ ዘርፎች ለግሉ ዘርፍ ክፍት መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ ዳንኤል ሀቼዝ በበኩላቸው የኅብረቱ ኢኒሼቲቭ የሆነው ግሎባል ጌትዌይ መሠረተ ልማትን፣ ንግድን፣ መልካም አስተዳደርን እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለመፍታት የመንግሥት እና የግል ተቋማትን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአውሮፓ ኅብረት ግሎባል ጌትዌይ በጋራ ከሚሠሩባቸው ዋና ዋና ሴክተሮች መካከል የኤሌክትሪክ ግሪድን ማዘመን፣ የገጠር ኤሌክትሪክ አቅርቦትን ማስፋፋት፣ እንዲሁም ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ወደሚያመነጭ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መሸጋገር ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም በንግድ እና ሎጅስቲክስ ዘርፍ፤ በኤክስፖርት ላይ የተመሠረተ ዕድገትን ማሳካት፣ መዋቅራዊ የንግድ ትሥሥር መፍጠር እና የሎጅስቲክስ ተወዳዳሪነትን ማሻሻል ከኅብረቱ ጋር በቅርበት የሚሠራባቸው ቁልፍ የትብብር መስኮች መሆናቸው በመድረኩ ተመላክቷል።
