የናሚቢያ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አዲስ ብሔራዊ አየር መንገድ እንደገና ለማቋቋም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እመየከረ መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች ገና በሂደት ላይ ያሉና ምንም ዓይነት ስምምነት ያልተደረገባቸው መሆናቸውን የገለጸው ሚኒስቴሩ የተለያዩ የቴክኒክ እና የስትራቴጂክ ትብብር አማራጮችን እየመረመረ መሆኑንም ነው ያስታወቀው፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እየተደረገ ያለው ንግግር አዲሱ ብሄራዊ አየር መንገድ ሲመሰረት በፋይናንስ ቀውስ ምክንያት የተዘጋው የሀገሪቱ የቀድሞ አየር መንገድ ዕጣ ፋንታ እንዳይደርሰው ለመከላከል መሆኑን ሚኒስቴሩ ማስታወቁን በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሚድያዎች ዘግበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የናሚቢያ መንግስት እያደረጉት የሚገኙት ንግግር የሚሳካ ከሆነ አየር መንገዱ ከአፍሪካ አገራት መንግሥታት ጋር በመተባበር ያቋቋማቸውና የባለቤትነት ድርሻ የያዘባቸው አየር መንገዶችን ቁጥር ከፍ ያደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቶጎ፣ የማላዊ፣ የዛምቢያ፣ የኮንጎ፣ የሞዛምቢክና የቻድ አየር መንገዶች ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡
