EthiopiaNews

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሞጆ በ60 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባውን ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፍያ የመጀመሪያ ምዕራፍ አስመረቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ የንግድ ቀጣና ስኬት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ፕሮጀክት በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ባለ 20 ጫማ ኮንቴነሮች የማስተናገድ አቅም ያላቸው ጣቢያዎችና ዘመናዊ መጋዘኖች ያሉት መሆኑን ገልፀው የደረቅ ብትን ጭነቶችን በሀገር ውስጥ እንዲታሸግ የሚያስችል ፣ የውጭ ምንዛሬን የሚቆጥብ እና የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የማዕከሉን የአሰራር ፍጥነት ለማሳደግ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተከለው የባቡር ላይ ክሬን ከባቡር መስመር የሚደረገውን የኮንቴነር ዝውውር በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያከናውን ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ አሰራሩ በዘመናዊ ዲጂታል መሰረተ ልማት የተሳሰረ በመሆኑ፣ ለተገልጋዮች ፈጣን እና አስተማማኝ አገልግሎትን ያሳልጣል ብለዋል።

ይህ ማዕከል ከኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ባሻገር ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን እና ኡጋንዳን የሚያስተሳስረው የ‘ደሱ’ ኮሪደር አካል መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ደረጃ ላይ ያላትን ስፍራ የሚያሻሽልና የቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስሯንም ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።