በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ፍትሃዊና ተደማጭነታቸውን ያረጋገጠ ውክልና ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህንድ ኒው ዴልሂ በመካሄድ ላይ ባለው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የማዕድን ሀብት ለኢነርጂ ሽግግር፣ ለላቀ ማኑፋክቸሪንግና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው አፍሪካ የበርካታ ማዕድናት ሀብት ባለቤት በመሆኗ የብሪክስ አባል ሀገራት የካፒታል፣ የቴክኖሎጂና የገበያ አማራጭ እንዳላቸው አንስተዋል።
እነዚህን ሀብቶች አቀናጅቶ ለመጠቀምና በጥሬ ሃብቱ ላይ እሴት ለመጨመር የብሪክስ ጥምረት ትልቅ እድልን የሚፈጥር መሆኑንም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በማዕድናት፣ በታዳሽ ኢነርጂ እና እያደገ ያለውን የኢንዱስትሪ አቅሟን መሰረት ባደረገ መልኩ አጋርነቶችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ትስስር ያላት አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገራቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝና አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስና የአፍሪካ ህብረት ያላቸው ትብብር ከአጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ድጋፏን እንደምትሰጥ የተገለጸ ሲሆን ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ጋር በተያያዘ ባነሱት ሀሳብ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓንና የውጭ ዕዳዋን ለማሸጋሸግ እየሰራች መሆኗም ተጠቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያላቸው ውክልና ፍትሃዊ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ውክልናው ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
