EthiopiaNews

ኢትዮጵያ ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ ዜጎቿን በዘላቂነት ለማቋቋም ያዘጋጀችውን የፕሮጀክት እቅድ የንጉሥ ሳልማን የሰብዓዊ ድጋፍና እርዳታ ማዕከል ሊደግፍ እንደሚችል መግለጹን በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

በሳዑዲ አረቢያ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና አምባሳደር ሙክታር ከድር ከማዕከሉ ዋና አስተዳዳሪና የንጉሣዊ ፍርድ ቤት አማካሪ ዶክተር አብዱላህ ቢን አብዱልዓዚዝ አል-ረቢዓህ ጋር በሪያድ መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ተዘጋጅቶ የቀረበው ፕሮጀክት ተብራርቷል።

ፕሮጀክቱ በ18 ወራት ውስጥ 30 ሺህ ተመላሾችን ለመደገፍ ያቀደ መሆኑን አምባሳደር ሙክታር ገልጸው ድጋፉ ከምግብና አስፈላጊ ቁሳቁስ በተጨማሪ ጊዜያዊ መጠለያ፣ የመጓጓዣ አገልግሎት፣ የሥነ-ልቦና ድጋፍ፣ እንዲሁም በሙያና በሥራ ፈጠራ ሥልጠና በማብቃት የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ ማስቻልን ያካተተ ነው ብለዋል።

አምባሳደሩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ብቻውን የተሟላ መፍትሔ እንዳልሆነ ጠቁመው ተመላሾች ከማኅበረሰባቸው ጋር ተቀናጅተው ዘላቂ የኑሮ መሠረት እንዲገነቡ ማስቻል የመልሶ ማቋቋሙ ዋና ዓላማ መሆኑን ማስረዳታቸውን ኤምባሲው ገልጿል።

ይህ አቀራረብ ተመላሾች ዳግም ለአደገኛና ሕገወጥ ፍልሰት የመጋለጥ ዕድላቸውን እንደሚቀንስም ሲጠቆም የማዕከሉ ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር አብዱላህ አል-ረቢዓህ በበኩላቸው የፕሮጀክቱን በጎ ዓላማ እንደሚደግፉ ገልጸው የማዕከሉ የቴክኒክ ቡድን የቀረበውን ሰነድ በዝርዝር በመገምገም ፕሮጀክቱን በምን መልኩ መደገፍ እንደሚቻል ዕቅድ እንደሚያዘጋጅ ማረጋገጣቸውን ኤምባሲው አስታውቋል።