በአዲስ አበባ ከተማ የ2019 የመማር ማስተማር ዘመን ነገ እንደሚጀመር የከተማዋ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
በአዲሱ የትምህርት ዘመን ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እና ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ለማድረግ አሰራር ተቀምጦ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን የገለጸው ቢሮው የተማሪዎችና መምህራን ተሳትፎ እንዲያድግ የሚያደርጉ ተግባራት ተጠናክረው በመሰራት ላይ እንደሚገኙም ገልጿል።
ለትምህርት ዘመኑ የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች፣ ዩኒፎርምና የምገባ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶችና ስርጭቶች የተከናወኑ ሲሆን ትምህርት ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ ነገ መስከረም 5 ቀን ለሚጀመረው የ2019 ትምህርት ዘመን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
