ትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በክልሉ አስቻይ ሁኔታ እስኪፈጠር በሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች በጊዚያዊነት እንዲመደቡ መወሰኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ።
ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት በትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችን ቅሬታ በተቀበሉት የውይይት መድረክ ላይ ነው።
ሚኒስትሩ ጦርነትና ግጭት ሸሽተው ከትግራይ የወጡ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ክልሉ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ትምህርት ሚኒስቴር መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት በኦንላይን እንደሚመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የተማሪዎቹን ምዝገባ ለማካሄድ ትምህርት ሚኒስቴር በበይነ መረብ የምዝገባ ስርዓት ማዘጋጀቱን የገለጹት ሚኒስትሩ ሁሉም በትግራይ ክልል ባሉ አራቱ ዩኒቨርስቲዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ትናንት ይፋ በተደረገው የኦንላይን መተግበሪያ ፕላት ፎርም በመሙላት እንዲመዘገቡ አሳስበዋል፡፡
በምዝገባው ወቅትም ተማሪዎች ከዚህ በፊት ይማሩበት የነበረውን ዩኒቨርስቲ፣ የትምህርት ዘመናቸውን እና የሚማሩበትን የትምህርት መርሐ ግብር በመግለጽ ባሉበት ቦታ ሆነው የዝውውር ፎርሙን በአጭር ጊዜ እንዲሞሉ አሳስበዋል።
መረጃው ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ ነው።
