EthiopiaNews

ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ ወደ 400 ሜጋ ዋት ልታሳድግ መሆኑ ተነገረ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይሄን ያለው ለኬንያ የሚቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።

በተቋሙ የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ደስታለም ኃይሉ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 200 ሜጋ ዋት ኃይል ለኬንያ እያቀረበች ነው ብለዋል።

ኃላፊው በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተከናወኑ ያሉ የቴክኒክና መሰል ሥራዎችን በማጠናቀቅ ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ የሚቀርበው የኃይል መጠን ወደ 400 ሜጋ ዋት ያድጋል ብለዋል።

ይሁንና ተጨማሪ ኃይል ከመላኩ በፊት የሙከራ ሥራውን የሚከታተል የጋራ የቴክኒክ ቡድን ወደ ሥራ መግባቱን ኢንጂነር ደስታለም ጠቁመዋል።

የኬንያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የግሪድ አለመረጋጋት እንዳይከሰት የጋራ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሙከራ ደረጃ 100 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለታንዛኒያ እያቀረበች በመሆኑ በኬንያና ታንዛኒያ መካከል ያለው የመሠረተ ልማት ማሻሻያ ሲጠናቀቅ መደበኛ የኃይል ሽያጭ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡መረጃው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘ ነው።