የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ አፈጻጸሙ የተቀዛቀዘው የሽግግር ፍትህ ሂደት ትግበራ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረቡ።
ዋና ኮሚሽነሩ ይሄን ጥሪ ያቀረቡት ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የእውነት፣ ፍትሕ፣ ካሳ እና ድጋሚ ያለመፈጸም ማረጋገጫ ጉዳዮች ልዩ ራፖርተር ጋር በጄኔቫ ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።
መንግሥት የብሔራዊ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን በሚያዝያ 2016 ዓ.ም እንዲሁም የትግበራ ፍኖተ ካርታውን በሰኔ 2016 ዓ.ም ማጽደቁን ያስታወሱት ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ህጋዊ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ አጠቃላይ፣ ሰለባ-ተኮር እና ታማኝነት ያለው የሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ እንዲኖር ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጿል።
ኢሰመኮ በኢትዮጵያ የብሔራዊ ምክክር መድረኩ ዋና ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ መንግሥት ሂደቱን ለማስፈጸም የገባውን ቁርጠኝነት እና በቅርቡ በክስ ሂደት ላይ የነበሩ ከ600 በላይ ግለሰቦችን መፍታቱን አድንቋል።
ኮሚሽነር ብርሃኑ መንግሥት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ዲሞክራሲያዊ ምህዳርን ለማስፋት እና የሰላም ግንባታ ጥረቶችን ለማስቀጠል የሚያግዙ ተመሳሳይ እርምጃዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
