EthiopiaNews

ትምህርት ሚኒስቴር ዘንድሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡ ተማሪዎች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ከተማሩበት ክልል ወይም ዞን ውጭ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ መደረጉን አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ይሄን ያለው የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የዩኒቨርሲቲ ምደባን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።

ሚኒስቴሩ 30 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ደግሞ በተማሩበት ክልል ወይም ዞን ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ መደረጉን ነው ያስታወቀው።

በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከ500 በላይ አጠቃላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በመጀመሪያ ምርጫቸው እንደተመደቡ የሚኒስቴሩ መግለጫ ያመለክታል።

በተጨማሪም የዞን፣ የወረዳ እና የትምህርት ቤት ስርጭት እና የፆታ ሚዛን በምደባው ሂደት ታሳቢ ተደርጓል ተብሏል።

ሚኒስቴሩ ተማሪዎች የተመደቡበትን ዩኒቨርስቲ በዚህ ማስፈንጠሪያ ማየት እንደሚችሉ ገልጿል፦ https://student.ethernet.edu.et/view-placement

በምደባው ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎች ቅሬታቸውን ለዚሁ ሲባል በተዘጋጀው የኦንላይን ሥርዓት ብቻ ይህ ምደባ ይፋ ከሆነበት ቀን ጀምሮ በ5 ቀናት ውስጥ አስፈላጊውን መረጃና ማስረጃ በማያያዝ እንዲያቀርቡም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

ቅሬታ ያላቸው ተማሪዎች በዚህ የቅሬታ ማቅረቢያ ማስፈንጠሪያ፦ https://student.ethernet.edu.et/complaints ማቅረብ እንደሚችሉ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ በአካል ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በመምጣት የሚቀርብ የምደባ ቅሬታ እንደማያስተናግድ ነው የገለጸው።