በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩና በሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በጊዜያዊነት ለመማር የተመዘገቡ ተማሪዎች ምደባ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በክልሉ በሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለተመደቡ አዲስ እና ነባር ተማሪዎች ከወቅታዊው ሁኔታ አንጻር የትምህርት ሂደታቸው እንዳይስተጓጎልና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲማሩ ሲባል ከክልሉ ውጭ ወደሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በጊዜያዊነት እንደሚመደቡም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡
ተማሪዎች በጊዜያዊነት የሚመደቡበት ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ እንደሚገለጽላቸው የጠቆመው ሚኒስቴሩ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሲስተካከልም መጀመሪያ ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው ትምህርታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግሯል።
በተለያየ ምክንያት በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን መቀጠል የሚፈልጉ ተማሪዎችን በተመለከተ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑም ነው የተገለጸው።
