ለኤች.አይ.ቪ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በምርመራ የመለየትና ወደ ሕክምና የማስተሳሰር ሥራ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ተብሏል፡፡
ይህ የተባለው የ2019 የመጀመሪያው ሁለት ወራት ተጋላጭ ተኮር የኤች አይ ቪ ምርመራ አገልግሎት የማሻሻያ ዕቅድ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተገመገሙበት ወቅት ነው፡፡
በጤና ሚኒስቴር የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፍቃዱ ያደታ በዚሁ ውቀት በ2019 የሥራ ዘመን ዋና ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል፤ ለኤች.አይ.ቪ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተጠናከረ ምርመራ ማድረግ እና ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የተገኘባቸውን ወደ ሕክምናና ክትትል ማስገባት ዋንኞቹ ናቸው ብለዋል።
በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በግልጽ በመለየትና ተጨባጭ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ፣ በ2030 ቫይረሱ የኢትዮጵያ የማኅበራዊ እና የጤና ችግር ወደማይሆንበት ለማድረስ በተቀናጀና በተጠናከረ መልኩ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
