በሚቀጥሉት 3 ቀናት በኢትዮጵያ በብዙ ቦታዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
በተለይ ምዕራብ አማራ፣ ሰሜን ሶማሌ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረሪ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰሜናዊ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።
እንዲሁም የምዕራብ፣ የምስራቅ፣ የደቡብ የሀገሪቱ ከፍተኛ ቦታዎችና የመካከለኛው ኦሮሚያና የሲዳማ ክልሎች ከቀላል እስከ ከባድ ዝናብ ይጠበቃል ብሏል።
በተጨማሪም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የምዕራብ ኦሮሚያና የሰሜን ሶማሌ ክልሎች አካባቢዎች ላይ እጅግ በጣም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የአየር ትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልና በሌሎች ስፍራዎች ላይ ደግሞ የተሻለ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የገለጸው ኢንስቲትዩቱ ነገር ግን በአፋር፣በትግራይና በጋምቤላ አብዛኛው ስፍራዎች ላይ ከ32 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ የሚሆን የሙቀት መጠን እንደሚኖርም አስታውቋል።መረጃው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ነው።
