InternationalNews

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሩዋንዳ የሚደገፈው የኤም 23 አማፅያን ቡድን በኮንጎ ማዕድን አውጪዎች ላይ አሰቃቂ ጥቃት በማድረስ የማዕድን ዘረፋ እየፈጸመ ነው አለ።

ተቋሙ በምስራቃዊ ኮንጎ ባደረገው ጥናት፣ አማፅያኑ በግፍ ከገደሏቸው 18 ማዕድን አውጪዎች በተጨማሪ በርካታ ሰራተኞችን በግዳጅ ሥራና በግርፋትና በእስራት ማሰቃየታቸውን እንዲሁም በግዳጅ ለውትድርና መመልመላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

እንደ ሪፖርቱ ገለፃ፣ የሩዋንዳ ባለስልጣናትና ነጋዴዎች ከኤም 23 አማፅያን ጋር በመተባበር የወርቅና የኮልታን ማዕድናት ከኮንጎ ድንበር ተሻግረው ወደ ሩዋንዳ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲገቡ የሚያመቻቹ ሲሆን፤ ይህም በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት የጦር ወንጀል ሊሆን የሚችል የሀብት ዘረፋ ነው።

የአምነስቲ ዋና ፀሐፊ አግነስ ካላማርድ፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሩዋንዳ ድርጊቱን ማቆሟን እስክታረጋግጥ ድረስ ከሀገሪቱ ማዕድናትን መግዛት እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በሞባይል ስልኮችና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ማምረቻነት የሚያገለግሉት እነዚህ ማዕድናት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ የሚሰራጩ በመሆናቸው፣ ማዕድናቱን የሚገዙ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በቀጠናው ለሚፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች ተባባሪ ሊሆኑ እንደሚችሉም አምነስቲ አስጠንቅቋል።