የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያላግባብ ወደ መሬት ባንክ ገብተዋል የተባሉ ይዞታዎችን ቅሬታ ሊመረምር መሆኑን ገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በ2015 ዓ.ም በተከናወነው ከተማ አቀፍ የባዶ ቦታ ልየታና ኦዲት ቆጠራ ወቅት ያላግባብ ወደ መሬት ባንክ ገብተዋል ተብለው ቅሬታ የቀረበባቸው ይዞታዎችን በአጠረ ጊዜ ውስጥ መርምሮ ምላሽ ለመስጠት የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱን ነው የገለጸው።
በወቅቱ በተከናወነው የባዶ ቦታ ልየታ 3ሺህ 744 ሄክታር ከህገ-ወጦች በመውሰድ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ በማድረግ የመንግስትና የህዝብ ንብረት እንዲጠበቅ ማደረጉን የገለጸው ቢሮው በዚህ እርምጃ ላይ ከ250 በላይ የሚሆኑ የቅሬታ ማመልከቻዎች መቅረባቸውንና ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰራም ጠቅሷል፡፡
ከሁሉም ክፍለ ከተሞች አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የቀረቡት ቅሬታዎች እንደየይዞታው ሁኔታ ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጠው የገለጸው ቢሮው የመንግስትና ህዝብ የመሬት ሀብት ከህገ-ወጥ ወረራ በመጠበቅ ሂደት ውስጥ፣ ህጋዊ ባለቤቶች የሆኑ አካላት ፍትህ እንዲያገኙና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የማስተካከያ ስራው በአስቸኳይ ይሰራል ነው የተባለው፡፡
