የአዲስ አበባ ፖሊስ በተደጋጋሚ ጊዜ ጨለማን ተገን በማድረግ የስርቆት ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በ20 አመት ከ10 ወር ፅኑ እስራት መቀጣቱን አስታወቀ፡፡
ደሳለኝ ጭናሾ የተባለው ተከሳሽ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመው በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ጦር ኃይሎች አካባቢ በተለያየ ቀናት መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
ተከሳሹ በአጠቃላይ 1 መቶ ሺህ 450 ብር የሚገመት ንብረት ሰርቆ ለመሰወር ሲሞክር በፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ መያዙን የፖሊስ መምሪያው አስታውቋል።
ግለሰቡ ከአንድ ምግብ ቤት ውስጥ የበር ቁልፍ ገንጥሎ በመግባት 18,000 ብር የሚገመቱ 3 የወንበር ዣንጥላዎችን መስረቁን ፖሊስ አስታውቋል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ /ቤት ኮልፌ ቀራንዮ ምድብ 3ኛ የወንጀል ችሎት የክስ መዝገቡን ከመረመረና የሰው ማስረጃዎችን ከአሰማ በኃላ ተከሳሹ በ20 አመት ከ10 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል።
ፖሊስ ህብረተሰቡ መሰል ወንጀል እንዳይፈፀምበት በንግድ ቤቶች አካባቢ አስተማማኝ ጥበቃ መቅጠርና የደህንነት ካሜራ መግጠም እንዳለበት አሳስቧል።
መረጃው ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘ ነው።
