InternationalNews

በጅቡቲ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ስደተኞችን የጫነ አንድ ጀልባ ሰጥሞ እስካሁን 139 ሰዎች መሞታቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።

አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ከ300 በላይ ሰዎችን አሳፍሮ እንደነበር የሚገመተውና ወደ የመን በመጓዝ ላይ የነበረው ይህ ጀልባ፣ አደጋ የገጠመው በጅቡቲዋ ኦቦክ አካባቢ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን እስካሁን በአደጋው 139 ሰዎች መሞታቸውን እና እስካሁን የት እንዳሉ የማይታወቁ ከ80 በላይ ሰዎች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡

የፍለጋና የነፍሥ ማዳን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ድርጅቱ ከአደጋ የተረፉት 82 ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልጿል።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ በአከባቢው ድንበር ለማቋረጥ ከሚክሩት መካከል አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የሚመጡ መሆናቸውን የጠቀሰ ሲሆን ከፈረንጆቹ 2025 ወዲህ ይህንን ጉዞ ለማድረግ ሲሞክሩ ከ900 በላይ ስደተኞች ህይወታቸውን ማጣታቸውንም አስፍሯል።

የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በዚህ አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፆ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል።